← ወደ መተግበሪያው ተመለስ

በዋሽንግተን መንጃ ፈቃድ እንዴት ማውጣት እችላለሁ? ደረጃ በደረጃ መመሪያ

መጨረሻ የተፈተሸው፦ ሕዳር 5 ቀን 2026 (እ.ኤ.አ.)

ይህ መመሪያ በዋሽንግተን ለመጀመሪያ ጊዜ መንጃ ፈቃድ ለሚያወጡ ሰዎች ነው። መረጃው የተወሰደው ከዋሽንግተን ግዛት የፈቃድ መስጫ መሥሪያ ቤት (DOL) ድረ-ገጽ ነው። Awra Permit Prep ከDOL ጋር ግንኙነት የለውም። ሕጎችና ክፍያዎች ሊቀየሩ ስለሚችሉ፣ ከመሄድዎ በፊት በ dol.wa.gov ያረጋግጡ።

ፈተናውን በየትኛው ቋንቋ ይወስዳሉ?

DOL የእውቀት ፈተናው (knowledge test) በ12 ቋንቋዎች እንደሚሰጥ ይዘረዝራል፦ እንግሊዝኛ፣ ስፓኒሽ፣ ዐረብኛ፣ ራሽያኛ፣ ዩክሬንኛ፣ ኮሪያኛ፣ ጃፓንኛ፣ ቪየትናምኛ፣ ፑንጃቢ፣ ታጋሎግ እና ሁለት ዓይነት ቻይንኛ። አማርኛ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የለም።

አንዳንድ የአሽከርካሪ ሥልጠና ትምህርት ቤቶች ግን ፈተናውን በአማርኛ አስተርጓሚ ይሰጣሉ። ይህ በሁሉም ቦታ ስለማይገኝ፣ ቀጠሮ ከመያዝዎ በፊት ትምህርት ቤቱን ይጠይቁ፤ ተጨማሪ ክፍያ እንዳለም ያረጋግጡ።

ፈተናውን በአማርኛ መውሰድ ከፈለጉ፣ ይህን መተግበሪያ ተጠቅመው ለፈተናው ዝግጁ ሲሆኑ፣ ኢሜይል ይላኩልን ወይም በስልክ ቁጥራችን ይደውሉልን። በአማርኛ የሚሰጥ ፈተና የሚያቀርቡ የአሽከርካሪ ሥልጠና ትምህርት ቤቶችን እንጠቁምዎታለን። ትምህርት ቤቶቹ ከ Awra Permit Prep ጋር ግንኙነት የላቸውም። ኢሜይል፦ support@awradrive.com፤ ስልክ፦ (206) 580-0633።

በDOL ቢሮ ለሚኖርዎት ቀጠሮ አስተርጓሚ ከፈለጉ፣ ቢያንስ ከ5 የሥራ ቀናት በፊት ወደ languageaccess@dol.wa.gov ኢሜይል ይላኩ።

በአማርኛ ማጥናት ይችላሉ። ፈተናውን በእንግሊዝኛ የሚወስዱ ከሆነ ግን ቃላቱን በእንግሊዝኛም አብረው ይማሩ። DOL የአሽከርካሪ መመሪያውን (Driver Guide) በአማርኛ በነጻ ያቀርባል።

የአማርኛውን መመሪያ ይክፈቱ

የትኛው መንገድ ለእርስዎ ነው?

ዕድሜዎ 18 ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ፦ የእውቀት ፈተናውንና የመንዳት ፈተናውን (drive test) በማለፍ መንጃ ፈቃድ ማግኘት ይችላሉ፤ የአሽከርካሪ ሥልጠና ኮርስ ወይም የለማጅ ፈቃድ (learner permit) አያስፈልግም። በሕዝብ መንገድ ላይ ለመለማመድ ከፈለጉ ግን የለማጅ ፈቃድ ያስፈልግዎታል።

ለውጥ፦ ከጥር 1 ቀን 2027 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ፣ መንጃ ፈቃድ በሚያገኙበት ቀን ዕድሜያቸው 18 የሆኑ የመጀመሪያ ጊዜ አመልካቾች የአሽከርካሪ ሥልጠና መውሰድ አለባቸው። ይህ ደንብ በየዓመቱ አንድ ዕድሜ እየጨመረ፣ በ2030 ከ22 ዓመት በታች ያሉትን ሁሉ ይመለከታል።

ዕድሜዎ ከ25 ዓመት በታች ከሆነ፦ በተጨማሪ ነጻ የኦንላይን ኮርስ (work zone and first responder course) ማለፍ አለብዎ። ከታች ደረጃ 6ን ይመልከቱ።

ዕድሜዎ ከ15 እስከ 17 ከሆነ፦ ወላጅዎ ወይም አሳዳጊዎ በኦንላይን ፈቃድ መስጠት አለባቸው።

ከኢትዮጵያ ወይም ከሌላ አገር መንጃ ፈቃድ ካለዎት፦ ወደ ዋሽንግተን ፈቃድ የሚለወጡት ከጥቂት አገሮች የመጡ ፈቃዶች ብቻ ናቸው፤ ኢትዮጵያ በDOL ዝርዝር ውስጥ የለችም። ስለዚህ እንደ አዲስ አመልካች ሁሉንም ደረጃዎች ማለፍ አለብዎ። ዋሽንግተንን እየጎበኙ ብቻ ከሆነ፣ የአገርዎን ፈቃድ እስከ 1 ዓመት መጠቀም ይችላሉ።

ከሌላ የአሜሪካ ግዛት የሚሠራ መንጃ ፈቃድ ካለዎት፦ ዕድሜዎ 18 ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ ፈተና አያስፈልግም። ወደ ዋሽንግተን ከገቡ በ30 ቀናት ውስጥ የዋሽንግተን ፈቃድ ማውጣት አለብዎ።

ዕድሜዎ 18 ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ፦ ደረጃዎቹ

ደረጃ 1፦ የWDL ቁጥር ያግኙ

License Express መለያ ይክፈቱ፣ ቅድመ-ማመልከቻ ይሙሉ፣ እና ባለ 12 አሃዝ የዋሽንግተን መንጃ ፈቃድ (WDL) ቁጥር ያግኙ። ይህ ቁጥር ለለማጅ ፈቃድ ማመልከቻና ለኦንላይን ኮርሱ ያስፈልጋል። ቁጥር እንዳለዎት ካላወቁ ወደ 360-902-3900 ይደውሉ።

ደረጃ 2፦ ያጥኑ

የአማርኛውን የአሽከርካሪ መመሪያ ያንብቡ፣ በልምምድ ጥያቄዎችም ራስዎን ይፈትኑ።

ደረጃ 3፦ የእውቀት ፈተናውን ይውሰዱ

በጸደቀ የፈተና ቦታ ቀጠሮ ይያዙ፤ ፈተናው በአካል ይወሰዳል። 40 ባለ ብዙ ምርጫ ጥያቄዎች አሉት፤ ለማለፍ 32 ትክክል (80%) ያስፈልጋል። ክፍያው እንደ ቦታው ይለያያል። ካላለፉ እንደገና ከመፈተንዎ በፊት የጥበቃ ጊዜ ሊኖር ይችላል። የማለፊያ ውጤቱ ለ2 ዓመት ይቆያል።

ደረጃ 4፦ ለመለማመድ ከፈለጉ የለማጅ ፈቃድ ያውጡ

የእውቀት ፈተናውን ካለፉ በኋላ ያመልክቱ። ክፍያው $35 ነው፤ ለ1 ዓመት ይሠራል፤ ሁለት ጊዜ ማደስ ይቻላል (በእያንዳንዱ $25)። ጊዜያዊ የወረቀት ፈቃድ ይሰጥዎታል፤ ካርዱ ከ2 እስከ 4 ሳምንት ውስጥ በፖስታ ይደርሳል። ፎቶ ያለው ፈቃድ ከፈለጉ የቢሮ ቀጠሮ ይያዙ።

ሲለማመዱ፦ ፈቃዱን ይዘው ይንዱ፤ ቢያንስ 5 ዓመት ልምድ ያለው፣ የሚሠራ መንጃ ፈቃድ የያዘ አሽከርካሪ ከፊት ተሳፋሪ ወንበር ላይ መቀመጥ አለበት፤ ከ911 በስተቀር ስልክ አይጠቀሙ።

ደረጃ 5፦ የመንዳት ፈተናውን ይውሰዱ

በፈተና ቦታ ቀጠሮ ይያዙ። ክፍያው እንደ ቦታው ይለያያል። ለማለፍ ከ100 ቢያንስ 80 ያስፈልጋል፤ ውጤቱ ለ1 ዓመት ይቆያል። እነዚህን ሁለት ነገሮች ካላመጡ መፈተን አይችሉም፦

የኪራይ መኪናም መጠቀም ይችላሉ። የመንዳት ፈተናውን በሌላ ቋንቋ ከፈለጉ፣ ቋንቋዎን የሚያቀርብ ትምህርት ቤት ይፈልጉ፤ ካላገኙ በDOL ቢሮ ቀጠሮ መያዝ ይችላሉ።

ደረጃ 6፦ ከ25 ዓመት በታች ከሆኑ ኦንላይን ኮርሱን ያጠናቅቁ

ነጻ ነው፤ 1 ሰዓት ገደማ ይወስዳል፤ መጨረሻ ላይ ፈተና አለው፤ በ14 ቋንቋዎች ይገኛል፤ በስልክም ይሠራል። የWDL ቁጥርና የWA.gov መለያ ያስፈልግዎታል።

ደረጃ 7፦ ለመንጃ ፈቃድ ያመልክቱ

ቀጠሮ ይዘው ወደ መንጃ ፈቃድ ቢሮ (driver licensing office) ይሂዱ። ፎቶ ያለው የዋሽንግተን የለማጅ ፈቃድ ካለዎትና ፈቃድዎ ካልታገደ ወይም ካልተሰረዘ፣ በኦንላይን ማመልከት ይችላሉ። በቢሮው የዓይን ምርመራ ይደረግልዎታል፣ ክፍያ ይከፍላሉ፣ ጊዜያዊ ፈቃድም ይሰጥዎታል። ካርዱ ከ7 እስከ 10 ቀናት ውስጥ በፖስታ ይላካል።

ክፍያ፦ መደበኛ መንጃ ፈቃድ $111 ለ6 ዓመት ወይም $131 ለ8 ዓመት። የተሻሻለ መንጃ ፈቃድ (EDL) $153 ለ6 ዓመት ወይም $187 ለ8 ዓመት። EDL ተጨማሪ ሰነዶች ይፈልጋል፤ የREAL ID መስፈርትን ስለሚያሟላ ለአሜሪካ ሀገር ውስጥ በረራ ይሠራል።

ምን ሰነዶች ይዘው ይሂዱ?

ኦሪጅናል ሰነዶችን ይዘው ይሂዱ፤ ፎቶ ኮፒ፣ ስካን ወይም ፎቶግራፍ አይቀበሉም። ከእነዚህ ጥምሮች አንዱ ማንነትዎን ለማረጋገጥ በቂ ነው፦

ብቻውን የሚበቃ፣ ለምሳሌ፦ የሚሠራ የአሜሪካ ፓስፖርት፣ ግሪን ካርድ፣ የሥራ ፈቃድ ካርድ (I-766)፣ የስደተኛ የጉዞ ሰነድ (I-571)፣ ፎቶና ፊርማ ያለው የዜግነት የምስክር ወረቀት፣ የአሜሪካ ግዛት መታወቂያ ወይም መንጃ ፈቃድ።

ዝርዝር A፣ ለምሳሌ፦ የአሜሪካ ቪዛ፣ የውጭ አገር ፓስፖርት ከ I-94 ወይም ከ I-551 ማኅተም ጋር።

ዝርዝር B፣ ለምሳሌ፦ የውጭ አገር መታወቂያ ወይም መንጃ ፈቃድ፣ የተረጋገጠ የልደት ምስክር ወረቀት፣ የሶሻል ሴኪዩሪቲ ካርድ፣ የተረጋገጠ የጋብቻ ምስክር ወረቀት።

የሶሻል ሴኪዩሪቲ ቁጥር (SSN) ካለዎት መስጠት አለብዎ፤ ከሌለዎት እንደሌለዎት የሚገልጽ ማረጋገጫ ይፈርማሉ።

እነዚህ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው፤ ሙሉው ዝርዝር በDOL ድረ-ገጽ ላይ አለ። ዕድሜዎ 25 ወይም ከዚያ በታች ከሆነ የወላጅዎን ወይም የአሳዳጊዎን ሰነዶች መጠቀም ይችላሉ። ሆን ብለው ሐሰተኛ ወይም አሳሳች ሰነድ ካቀረቡ ለ1 ዓመት እንደገና ማመልከት አይችሉም። EDL የተለየ የሰነድ ዝርዝር አለው።

ሙሉውን ዝርዝር ይመልከቱ

ከፈተናው በፊት ይለማመዱ

ነጻ ጥያቄዎችን ይሞክሩ፤ ምዝገባ አያስፈልግም። ቋንቋውን በአማርኛና በእንግሊዝኛ መካከል መቀያየር ይችላሉ፤ ከእያንዳንዱ መልስ በኋላም ማብራሪያ ያገኛሉ። ጥያቄዎቹ በአሽከርካሪ መመሪያው ላይ የተመሠረቱ የልምምድ ጥያቄዎች ናቸው፤ ትክክለኛዎቹ የፈተና ጥያቄዎች አይደሉም።

ነጻ ጥያቄዎችን ይሞክሩ